Friday, January 24, 2014

ተሳል


    የተለያዩ ጽሁፎችን ሳገላብጥ ይህንን ጽሁፍ አገኘሁ ። ጽሁፉ በ አንድ ወቅት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት  በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የጻፈው ነው ይህንን ጽሁፍ ካነበብኩት በሁዋላ ለሁሉም ሰው ትምህርት ሊሰጥ ይችላል በሚል እንድታነቡት እና እንዲወያዩበት አቅርቤላችሁዋለሁ ።
አማካሪ ጥሩ የሚባሉ ነገሮችን ፈልጎ ማቅረቡን ይቀጥላል ። የተለያዩ ሃሳቦች ካሎት ሃሳብዎን በሃሳብ መስጫ(comment ) ላይ ያኑሩልን !

 ተሳል



ልጁ አባቱን ሊጠይቅ ነበር የመጣው፡፡ ሐኪም ነው፡፡ ሐኪም ደግሞ በመንደሩ የተከበረ ነው፡፡ እርሱ መጣ ሲባል በመንደሩ የነበሩ ሕሙማን ሁሉ የአባቱን ቤት ሞሉት፡፡ ብዙዎቹ እንዲሁ አይቶ በሽታቸውን የሚያውቅላቸው ስለሚመስላቸው ‹‹ምንዎትን ነው ያመመዎት›› የሚለው ጥያቄ ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ ‹‹ያመመኝን ካወቅኩትማ ምን ችግር ነበረበት፤ በሽታዬን ሊነግረኝ አዶለም እንዴ ሐኪም የሆነው›› ይሉታል ከቤት ከወጡ በኋላ፡፡
አባቱ አንድ ቀን እንዲህ አሉት ‹‹ድሮ ትዕግሥተኛ ነበርክ፤ አሁንኮ በረባ ባልረባው ትነጫነጫለህ፤ ያሳደጉህን ሠፈርተኞችህን ሁሉ ትሰድባቸዋለህ፡፡ ደግሞ አንዳንዱ በሽታ አዲስ ሆኖብሃል፡፡ ድሮኮ ‹እጁ መድኃኒት ነው›› ትባል ነበር፡፡ ቀንና ሌሊት ሠርተህ አይደክምህም ነበር፡፡ እንግዳ ነገር እንኳን ሲገጥምህ ጓደኞችህን ለመጠየቅ በስልክ ስታጨናንቃቸው ነበር የምታመሸው፡፡ አሁን ምነው ያለ ጊዜህ አረጀህ ልጄ›› አሉት፡፡
የአባቱ ትዝብት ያልጠበቀው ነው፡፡ ግን በትክክል ነው የገለጡት፡፡ አሁን በቀላሉ ይታክተዋል፡፡ እንዲያውም ያሳደጉት የሠፈሩ ሰዎች ሆነውበት እንጂ ዞር ብሎ ባያያቸው በወደደ፡፡ ለነገሩ በመሥሪያ ቤቱም አካባቢ እንዲሁ ነው የሚሉት፡፡ ‹ሆስፒታሉን ትቶ ኤን ጅኦ ከገባ በኋላ ነገር ዓለሙን ትቶታል› የሚሉት ብዙዎች ናቸው፡፡ ‹አሁንማ አለቃ እንጂ ሐኪም አይደለም፤ ባለ ገንዘብ እንጂ ባለ ዕውቀት መሆኑ ቀርቷል፤ በድሮው ስሙ ነው ያለው›› ይሉታል፡፡
አሁን አዲስ ነገር የሆነበት አባቱም ተመሳሳይ ነገር መናገራቸው ነው፡፡ ለወትሮው ‹ዓይኔ ብርሃኔ› እያሉ ለመጣ ለሄደው ስለ እርሱ እየተረኩ ሰው የሚያሰለቹት አባቱ ዛሬ ለራሱ ቅሬታቸውን መንገራቸው አዲስ ታሪክ ሆኖበታል፡፡ መንደርተኞቹን ካከመ በኋላ በቤት ውስጥ ቡና ተፈልቶ ምርቃትና ምስጋና ይዥጎደጎድ እንዳልነበረ፣ ዛሬ ‹‹ምነው ልጄ›› የሚል ስሞታ መጣበት፡፡
ለአባቱ አልመለሰላቸውም፡፡ ለተወሰነ ጊዜ እርሳቸውን ካዳመጣቸው በኋላ ቀጥሎ ውስጡን ነበር የሚያዳምጠው፡፡ ሥራ እንጨት እንጨት ብሎታል፡፡ ሞያው ሐኪም መሆኑ ትዝ የሚለው ሰዎች ‹ዶክተር› ብለው ሲጠሩት ነው፡፡ ስብሰባው፣ ሴሚናሩ፣ ደብዳቤው፣ ንግግሩ ሁሉ የቢሮክራሲ እንጂ የሞያ አይደለም፡፡ የሚያደንዝ እንጂ የሚስል አልሆነም፡፡ የሚያስረሳ እንጂ የሚያነቃ አልሆነም፡፡
‹‹ልጄ›› አሉት አባቱ ከረዥም ዝምታ በኋላ፡፡
‹‹አቤት›› አላቸው ከተጓዘበት በፍጥነት ተመልሶ፡፡
‹‹ለመሆኑ ሞያህን ለማሳደግ ልምምድ ታደርጋለህ? ከወዳጆችህ ጋር ትወያያለህ? ሌላ ቦታ ሄደህ ልምድ ትቀስማህ? ታነባለህ? እንደገናስ ትማራለህ? በጎንደር መምህር ኤስድሮስ የሚባሉ መምህር ነበሩ አሉ፡፡ መጻሕፍቱን ሁሉ መርምረው ትርጓሜ አቅንተው ሲያስተምሩ ኖሩና ‹ምናልባት ያልደረስንበት አዲስ ነገር ቢኖርስ› ብለው በዚያ በጣና ገዳማት ውስጥ ገብተው መጻሕፍቱን ሁሉ ሲያገላብጡ ኖሩ አሉ፡፡ እውነትም ያልደረሱበት ብዙ ነገር ቢያገኙ ተማሪዎቻቸውን እንደገና ጠርተው ‹እኔም ያላወቅኩት እናንተም ያልተማራችሁት አዲስ ነገር አግኝቻለሁና ኑ እንደገና እንማር› ብለው ሰበሰቧቸው፡፡ እሺ ብለው ለአዲስ ዕውቀት የመጡ አሉ፡፡ እምቢ ብለው በቀድሞው ብቻ የቀሩ አሉ፡፡ እሺ ብለው የመጡት የሄዱበት መንገድ ‹የታች ቤት ትርጓሜ› ተባለ፡፡ እምቢ ብለው የቀሩት የሄዱበት መንገድ ደግሞ ‹የላይ ቤት ትርጓሜ› ተባለ፡፡ ለመሆኑ አንተስ ምናልባት ያልደረስኩበት ነገር ቢኖር፤ አዲስ የመጣ ነገር ቢኖር፤ ማወቅ ሲገባኝ ሳላውቀው የቀረሁት ነገር ቢኖር ብለህ አስበህ ታውቃለህ? ዕውቀትኮ ካልጨመሩበት አንድም እየዛገ አንድም እየጠፋ ይሄዳል፡፡ ትዶለዱማለህ ልጄ፡፡ አንድ ምሳሌ ልንገርህ ፡-
‹ሰውዬው ሥራ ፍለጋ ሲንከራተት ወደ አንድ የጣውላ ፋብሪካ ይደርስና ይጠይቃል፤ ሰውነቱ ግዙፍና ጠንካራ መምሰሉን ይመለከትና ባለቤቱ እንዲገባ ይጋብዘዋል፡፡ ያላቸው የሥራ መስክ እንጨት ቆራጭነት መሆኑን ይነግሩታል፡፡ ሰውዬውም ያገኘውን ሁሉ ለመሥራት ታጥቆ የተነሣ ነበርና ተቀበለ፡፡ የተወሰነ ሰዓት በመጥረቢያ እንዴት ዛፍ እንደሚቆረጥ አሠለጠኑትና ወደ ሥራው ተሠማራ፡፡ ክፍያው በቆረጠው ዛፍ ልክ ነበር፡፡
በመጀመሪያው ቀን ሃያ ዛፍ ቆረጠና ጥሩ ክፍያ አገኘ፡፡ በዚህ ደስ ብሎት በማግሥቱ ተነሥቶ ወደ ሥራው ገባ፡፡ በዚያ ቀንም ዘጠኝ ዛፍ ቆረጠ፡፡ በሦስተኛው ቀን ሰባት፣ በአራተኛው ቀን ስድስት፣ በአምስተኛው ቀን አምስት፣ በስድስተኛው ቀን አራት ቆረጠ፡፡ ድካሙ ያው ነው፡፡ የሚቆርጠው ዛፍ ግን እያነሰ ሄደ፡፡ ዛፉ ሲያንስም ክፍያው አነሰው፡፡ ለዕለት ምግቡ እንኳን አልበቃው አለ፡፡ በመጨረሻም ተስፋ ቆረጠ፡፡
ወደቀጠረው ሰው ዘንድ ሄደና ሥራን ለማቆም እንደሚፈልግ ነገረው፡፡ ‹‹ለምን ታቆማለህ፤ ክፍያው አልተስማማህም?›› አለው፡፡ ‹‹ሂሳቡ በቂ ነው፤ ነገር ግን ብዙ ዛፍ በአንድ ቀን ለመቁረጥ አልቻልኩም፡፡ ካደር አደር እየቀነስኩ መጣሁ፡፡ በዚያውም ልክ የሚከፈለኝ ገንዘብ እየቀነሰ ሄደ፡፡ አሁን ችግር ውስጥ ከመውደቄ በፊት ሥራውን ለማቆም ወሰንኩ›› አለው፡፡
አሠሪውም ‹በመጀመሪያ ስንት ዛፍ ነበር የቆረጥከው?›› አለው፡፡
‹‹አሥር››
‹‹በመጨረሻስ?››
‹‹አራት››
‹‹ለመሆኑ መጥረቢያውን ስለህው ታውቃለህ?›› አለው፡፡
‹‹ኧረ በጭራሽ›› አለ ቆራጩ፡፡
‹‹ታድያ ምን አድርግ ነው የምትለው፡፡ በመጀመሪያ ቀን የተሳለ መጥረቢያ ሰጥተንህ ስለነበር አሥር ቆረጥክበት፡፡ በየቀኑ በሠራህበት ቁጥር እየዶለዶመ ስለሚሄድ በመጨረሻ አራት ላይ ደረስክ፡፡ ብትቀጥል ደግሞ አንድ ዛፍ መቁረጥ የማትችልበት ደረጃ ላይ ትደርስ ነበር፡፡ በሠራህ ቁጥር መጥረቢያውን እንደገና መሳል አለብህ፡፡ ሁልጊዜም አዲስ ሆኖ ሌላ ዛፍ ለመቁረጥ እንዲችል በየጊዜው መሳል አለብህ፡፡ አሁንም ሂድና እንደዚያ አድርግ›› ብሎ አሰናበተው፡፡
‹‹አየህ ልጄ አእምሮም እንደዚያው ነው፡፡ በየጊዜው መሳል ይፈልጋል፡፡ እንደገና መማር፣ እንደገና ማንበብ፣ እንደገና መሠልጠን፣ እንደገና ሞያ መለማመድ ይፈልጋል፡፡ ያለበለዚያማ የዛሬ ስንት ዓመት በተማርከው ከተቀመጥክ ትዶለዱማለህ፤ መጥረቢያውኮ አልጠፋም፡፡ አልተለወጠም፡፡ አሁንም መጥረቢያ ነው፡፡ ግን ስለቱ ቀነሰና አገልግሎቱ ደከመ፡፡ አንተምኮ አሁንም ሐኪም ነህ፤ አልተለወጥክም፡፡ ግን ትዶለዱምና ውጤታማነትህ ይቀንሳል፡፡
ስለዚህ ልጄ ሂድና ተሳል፤ በየጊዜውም ተሳል፤ በሠራሀ ቁጥር ተሳል፤ አዲስ ዛፍ ለመቁረጥ መጥረቢያው መሳል እንዳለበት ሁሉ፤ አዲስ ችግር ለመፍታት፣ አዲስ ሃሳብ ለማመንጨት፣ አዲስ መንገድ ለማግኘት፣ አዲስ ሕመም ለመፈወስ እንድትችል ሂድና አንተም ተሳል›› አሉት፡፡
ጉልበታቸውን ስሞ ቀና ሲል ግንባሩን ሳሙት፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት የወጣ ነው

1 comment:

  1. This is really Nice........ WoW its a nice publication and collecting knowledge should be endless Thank you Daniel!

    ReplyDelete