Thursday, March 7, 2019

ድንች ኃይል ይሰጣል


ድሮ ከልጆች ጋር ስንጫወት ተመትተን ከመጣን ወላጆቻችን ይቆጣሉ፡፡ ‹ለምን ታለቃቅሳለህ› የሚለው የመጀመሪያ ቁጣቸው ነው፡፡ ወይ እዚያው ታግለህ አሸንፈህ መምጣት ነው፤ አለያም ደግሞ መሸነፍህን አምነህ በቀጣይ እንዴት እንደምታሸንፍ ማሰብ ነው፡፡ ማለቃቀስ መፍትሔ አይሆንም፡፡
ሦስተኛ ክፍል እያለሁ ሙሉጌታ የሚባል ልጅ እኛ ክፍል ነበረ(ስሙ ተለውጧል)፡፡ ሙሉጌታ እንደ ጸጋዬ የሚፈራው አልነበረም፡፡ ልጆቹም ተንኮለኞች ናቸው መሳቅ ሲፈልጉ ሙሉጌታና ጸጋዬን ማጋጠም ይወዳሉ፡፡ ጸጋዬ ወፍራም ነው፡፡ ሙሉጌታን ከመሬት ጋር ይሰፋዋል፡፡ ሙሉጌታ ሦስት ጊዜ ይቀጣል፡፡ ጸጋዬ ያደባየዋል፡፡ ልጆቹ ይስቁበታል፡፡ እናቱ ደግሞ ‹እያለቃቀስክ አትምጣ፣ የአንተ እጅስ ሙቅ ይዟል ወይ!› ብለው ይገርፉታል፡፡
አንድ ቀን የሳይንስ አስተማሪያችን ስለ ኃይል ሰጭ ምግቦች አስተማረን፡፡ ድንች ኃይል እንደሚሰጥ ከነ ሥዕሉ አሳየን፡፡ የሙሉጌታ ዓይኖች በሩ፡፡ ልቡ ሞቀ፣ አዲስ ሐሳብ የተገለጠለት መሰለው፡፡ እናቱ የድንች ነጋዴ ናቸው፡፡ ቤቱ የቅዳሜ ገበያ ፊት ለፊት ነበር፡፡
ቤቱ እንደገባ ድስት ሙሉ የድንች ቅቅል በሚጥሚጣ አስቀርቦ ራቱን በላ፡፡ ጠዋትም ቁርሱ እርሱ ነበር፡፡ ከዳንቴል በተሠራው ቦርሳው አንድ አምስት ድንች ይዞ መምጣቱ ትዝ ይለኛል፡፡


በዕረፍት ሰዓት ሙሉጌታ እጅጌውን እየሰበሰበ መጣ፡፡ ‹ዛሬ ከጸጋዬ ጋር መጋጠም እፈልጋለሁ› አለ፡፡ ተማሪዎቹ ሁሉ የሙሉጌታን ኮስማና ሰውነት እያዩ ደነገጡ፡፡ ምን ተፈጠረ? ‹ትናንት የተማርነውን ታስታውሳላችሁ› አለ ሙሉጌታ፡፡ ሁላችንም ከብበን እናየዋለን፡፡ ‹ድንች ኃይል ይሰጣል› አለ ሙሉጌታ፡፡ ከዚያም በቦርሳው ያመጣውን ቅቅል ድንች ፈረካክሶ አከፋፈለን፡፡ እየበላን ራሳችንን በአድናቆት ነቀነቅንለት፡፡ ‹ትናንትና ዛሬ ጠዋት አንድ ድስት ሙሉ ድንች ነው የበላሁት› አለ ሙሉጌታ፡፡ እኛም በተማርነው መሠረት የሠፈረበትን ኃይል ለማወቅ መላ ሰውነቱን አየነው፡፡ አንድ ድስት ሙሉ ድንች ከበላማ ማን ይችለዋል፡፡ ለራሳችንም ፈራን፡፡ ልጆች ነበርንና አንዳች ኃይል ከድንች ማግኘቱን አመንን፡፡ እናቱ ድንች እንደሚነግዱ እናውቃለን፡፡ ደግሞ አስተማሪያችን ከድንች ኃይል እንደሚገኝ በሥዕል ጭምር አሳይተውናል፡፡
‹ወይኔ ጸጋዬ አለቀለት› አልን፡፡ ጸጋዬ መጣ፡፡ የተወሰኑ ልጆች ጠጋ ብለው የሆነው ነገር ነገሩት፡፡ ጸጋዬ ደነገጠ፡፡ እነ ሙሉጌታ ቤት ድንች እንደ ልብ መሆኑን ያውቃል፡፡ ድንች ደግሞ ኃይል ይሰጣል፡፡ ‹ግጠመው፣ ግጠመው› አልነው ተሰብስበን፡፡ ጸጋዬ ፈራ፡፡ ሙሉጌታ ትከሻውን ሰበቀ፡፡ ‹ፈሪ! ፈሪ! ፈሪ! ተንፈርፈሪ› ጩኸትና ጭብጨባ፡፡ ጸጋዬ አንገቱን ሰብሮ መጣ፡፡ ሙሉጌታ እግሮቹን አንፈራጠጠ፡፡ ተጋጠሙ፡፡ ሙሉጌታ በዚያች ቀጫጫ ሰውነቱ ጸጋዬን አነሣው፤ ተሸከመው፡፡ መሬት ላይ ጣለው፡፡ ሆሆሆሆሆሆ፤ ትምህርት ቤቱ አበደ፡፡
ጉድ ተባለ፡፡ መሬቱን በእግራችን እየረገጥን አጨበጨብንለት፡፡ የሙሉጌታ አልቃሻነት ከዚያ በኋላ ቀረ፡፡
ዛሬ ሳስበው ሙሉጌታ ኃይል ያገኘው ከበላው ድንች አይመስለኝም፡፡ ‹ድንች ኃይል ይሰጣል› ከሚለው ትርክት እንጂ፡፡ ጸጋዬንም ያስደነገጠው ያ ነው፡፡ የሙሉጌታ ሰውነት አልተለወጠም፡፡ ያው ቀጫጫው ሙሉጌታ ነው፡፡ እምነቱ ግን ተቀይሯል፡፡ ጸጋዬን ሲያየው እንዴት እንደሚሮጥ ነበር የሚያስበው፡፡ ለዚህ ነው ምንጊዜም ተመትቶ የሚያለቅሰው፡ ያውም ሮጦም ፣ ተመትቶም፣ ተሰድቦም፡፡
ዛሬ ግን ለማሸነፍ እንጂ ለማልቀስ አልመጣም፡፡ ሙሉጌታ ከዚህ በፊት እንዲህ አድርገኸኝ፣ እንዲህ ሆኜ፣ እንዲህ ተደርጌ እያለ ቢያላዝን ኖሮ በአእምሮው የሚመጣው ሽንፈቱ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ድንቹን ብቻ ነው ያሰበው፡፡ ‹ድንች ኃይል ይሰጣል፡፡›
የልቅሶ ፖለቲካ የአሸናፊዎች ፖለቲካ አይደለም፡፡ በእዬዬ የሚሸነፍ የለም፡፡ እዬዬ ልብ ያደክማል፤ ወኔን ይሰልባል፡፡  በዚህ ዓለም እንደ አይሁድ በየዘመናቱ መከራን የተቀበለ ሕዝብ የለም፡፡ ዘራቸውን ከምድረ ገጽ ሊያጠፋ የሚችል ሥራ ተሠርቶባቸዋል፡፡ ግን ዛሬም በኃያልነት አሉ፡፡ ለምን? አንዱ ምክንያታቸው እዬዬን አለመውደዳቸው ነው፡፡ ታላቅነታቸውን፣ ምርጥ ሕዝብነታቸውን፣ ክብርና ገናናነታቸውን፣ በመከራ ውስጥ እንኳን ጽናትና ቆራጥነታቸውን ነው የሚተርኩት፡፡ ሥነ ልቡናቸው በአሸናፊነት እንጂ በአልቃሻነት ላይ አልተመሠረተም፡፡ ጸጋዬ ወፍራም ነው ያንደባልለናል፤ አይሉም - ድንች ኃይል ይሰጣል ብለው ነው የሚያምኑትም፣ የሚነሡትም፡፡ እንደ ሙሉጌታ በቁጥርም በመጠን አንሰው፣ እንደ ጸጋዬ የሚበዙትንና የሚበልጡትን ያሸነፉት በዚህ ሥነ ልቡና ነው፡፡
አሁን አሁን የኢትዮጵያዊነት ሥነ ልቡና የእዬዬ ሥነ ልቡና እየሆነ ነው፡፡ እናቴ ኢትዮጵያ ግን እንደ ሙሉጌታ እናት ‹ተመትተህ መጥተህ አታለቃቅስ› ትላለች፡፡ ጸጋዬ እንዲህ አደረገኝ እያለ የሚያለቃቅስ ልጅ አትወድም፡፡ ወይ በርትተህ ተጋፈጥ፣ ወይ ተቀብለህ ዝም በል፡፡ የእርሷ ወታደሮች ቁስላቸውን አሥረው የሚዋጉ እንጂ ቁስላቸውን እያዩና እያሳዩ የሚያለቃቅሱ አይደሉም፡፡ የእዬዬ ሥነ ልቡና ችግርህን ቀና ብለህ እንድታዬው ያደርግሃል፡፡ ችግርህ ከላይ አንተ ከታች ከሆንክ ደግሞ አቋምህ የተሸናፊነት ይሆናል፡፡  
አፍሪካ አሜሪካውያንን የጎዳቸው አንዱ ሥነ ልቡና ይሄ ነው ይባላል፡፡ አዘውትረው የደረሰባቸውን ጭቆና፣ ያጋጠማቸውን መገፋት፣ የሆነባቸውን ግፍ ያስቡታል፤ ይተርኩታል፤ ፊልምና ዘፈን ያደርጉታል፤ ይቆዝሙበታል፡፡ ስላላቸው ዐቅም፣ ኃይል፣ ችሎታ፣ ልዩ ጸጋና ብርታት አይተርኩም፡፡ የታሪክ እሥረኛ የመሆን ዕጣ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ትርክታቸው ሊያደርጉት በሚችሉት ላይ ሳይሆን ከዚህ በፊት በሆነባቸው ላይ ይመሠርቱታል፡፡ ያንን የኋላውን ሲተርኩት እንኳን በጀግንነት፣ በጽናትና በቆራጥነት መንፈስ ሳይሆን በተሸናፊነት መልኩ ነው፡፡
ትናንትም ሆነ ዛሬ ችግሮች ነበሩ፤ ይኖራሉ፡፡ እንደ ሕዝብ እንደ ሀገር ያጋጠመን ነገር ይኖራል፡፡ ወሳኙ ነገር ግን ምን ገጠመን ሳይሆን እንዴት እንተርከዋለን ነው፡፡ it is all about the story. እንዲሉ፡፡ መቱኝ፣ ተመታሁ፣ መታቱኝ፣ አስመቱኝ፣ እያሉ ማለቃቀስ ወኔን ይሰልባል እንጂ ጀግናን አያፈራም፡፡ እዬዬ ለአሸናፊነት አያበቃም፡፡ ቁስልን ማከም እንጂ ማከክ አያድነውም፡፡ የጀግና ሕዝብ ሥነ ልቡና ‹ሙሉጌታ ወፍራም ነው፣ ከዚህ በፊትም መቶኛል› በሚል ሳይሆን ‹ድንች ኃይል ይሰጣል› በሚል የሚገነባ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ማን ነህ? አይደለም፡፡ ምን ታምናለህ? ነው፡፡ ዳዊትን በጎልያድ ፊት ያቆመው እምነቱ ነው፡፡ ዐቅሙ አይደለም፡፡
ድንች ኃይል ይሰጣል፡፡ እዬዬ ልብ ያደክማል፡፡ 

ዳንኤል ክብረት



No comments:

Post a Comment