(ኣንድ)
በቀደም ለት ፤ ከቦሌ መድሃኒያለም ቅጽር ፊትለፊት ኣንድ ኣንድ ትንሽ ድንቡሼ ህጻን ቁጭ ብሎ ያንጎላጃል፡፡ ድንገት ብንን ኣለና በደስታ እየጮከ ሮጦ ካንድ ኣዳፋ ከለበሰ ጎልማሳ እግር ሥር ተጠመጠመ፡፡ ሰውየው የልጁ ኣባት መሆኑን ገመትኩ ፡፡ ኣባትየው የልጁን ኣዳፋ እጀጠባብ ኣወለቀለትና በፌስታል ይዞት የመጣውን ሌላ ውራጅ ሸሚዝ ኣለበሰው፡፡ ከዚያም የተፈነከተ ሸንኮራ ኣውጥቶ ሰጠው፡፡ ልጁ ፊት ላይ ያየሁት ንጹህ ደስታ እንዴት ልቤን እንደበላኝ!
(ድሮ፤ ሰዎች ለማኝ የሚሆኑት በስንፍና ወይም በባህል ጫና ምክንያት ይመስለኝ ነበር፡፡ምንኛ ተሳስቻለሁ!! ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንክሮ የሚሠራ ሰው ጠንክሮ ይቸገራል፡፡ለዚህ ምስክሬ ያዲሳባ ሎተሪ ኣዟሪ ህጻናት ናቸው፡፡ ኣንድ ትንሽ ልጅ ሎተሪ ኣዟሪ ኣንድ ሎተሪ ሲሸጥ ቀጣሪው መሥርያ ቤት የሚከፍለው ኣስራ ኣምስት ሳንቲም ብቻ ነው ቢባል ማን ያምናል፡፡ ይሄ ልጅ ኣዲስ ኣበባን ቀኑን ሙሉ በባዶ እግሩ ሲያካልል ውሎ በተኣምር መቶ ትኬት ቢሸጥ የሚያገኘው ኣስራ ኣምስት ብር ብቻ ነው፡፡ኣስራ ኣምስት ብር እዛው ቦሌ መድሃኒያለም ያንድ ስኒ ቡና በላይ መግዛት የመግዛት ኣቅም የለውም ፡፡)
የመድሃኒያለምን ኣስፓልት ኣቋርጨ ወደ ኤድና ሞል ህንጻ ዘው ብየ ገባሁ፡፡በህንጻው ምድር ቤት በሚገኘው
የህጻናት ማጫወቻ ክፍል ውስጥ የሃብታም ልጆች ካንዱ ማሽን ወደ ኣንዱ ማሽን እየዘለሉ እንደ ወፍ ጫጩት ይንጫጫሉ፡፡
ኣንድ ልጅ “ ስካይ ፎክስ” የተባለውን ኣሻንጉሊት ሂሊኮፍተርን እያበረረ ይሞላቀቃል ፡፡ ኣባቱ ደብተር
የሚያክል ሞባይል ደቅኖ ልጁን ኣሁንም ኣሁንም ፎቶ ያነሳዋል፡፡ ጠጋ ኣልኩና ለማሽኑ የሚከፈለውን ዋጋ
ኣጠናሁ፡፡ለሦስት ደቂቃ ሃያ ኣራት ብር እንደሚያስከፍል ተረዳሁ፡፡ ልጁ ሰላሳ ደቂቃ ሂሊኮፍተሩን ቢያበር ኣባትየው
ስንት እንደሚያወጣ ኣሰብኩና ኣማተብኩ፡፡
የሃብታም ልጆች በብር ሲጫወቱ፤ የድሃ ልጆች ደግሞ የኣስራ ኣምስት ሳንቲም ድህነት ሲጫወትባቸው ታዝቤ ጉዞየን ቀጠልኩ፡፡
በኣዲስ ኣበባ ኣስፓልት ላይ በእግሬ በተንሸራሸርኩ ቁጥር የትቦታ እንዳነበብኩት የረሳሁት ጥቅስ ይመጣብኛል፡፡ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፤“ሰው በዚህ ኣለም ሲኖር ወይ ልቡ በጣም ይጠነክራል፡፡ኣለያም ልቡ ይሰበራል”
(c) Bewketu Seyoum
የሃብታም ልጆች በብር ሲጫወቱ፤ የድሃ ልጆች ደግሞ የኣስራ ኣምስት ሳንቲም ድህነት ሲጫወትባቸው ታዝቤ ጉዞየን ቀጠልኩ፡፡
በኣዲስ ኣበባ ኣስፓልት ላይ በእግሬ በተንሸራሸርኩ ቁጥር የትቦታ እንዳነበብኩት የረሳሁት ጥቅስ ይመጣብኛል፡፡ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፤“ሰው በዚህ ኣለም ሲኖር ወይ ልቡ በጣም ይጠነክራል፡፡ኣለያም ልቡ ይሰበራል”
(c) Bewketu Seyoum
No comments:
Post a Comment