ዕቃ ለማውጣት ቦሌ ወደሚገኘው የካርጎ ተርሚናል ሄጃለሁ፡፡ መቼም ዘመድ ውጭ ሀገር
ያለው ሰው ደጋግሞ የሚሄደው አንድም ለወዳጁ እድሜ ከጤና ለመለመን ቤተ ክርስቲያን፣ አንድም የተላከለትን ዕቃ ለመውሰድ ካርጎ
ተርሚናል፣ አንድም የዓመት በዓል ብር ለመቀበል ባንክ ቤት ነው፡፡
ወረፋውን ጠብቄ መስኮቱ ጋ ደረስኩና ስሜን አስመዘገብኩ፡፡ እስክትጠራ ጠብቅ ተብዬም
ወንበር ፈልጌ ተቀመጥኩ፡፡ ከጎኔ አንድ ጎልማሳ ተቀምጦ ይቁነጠነጣል፡፡ አንዴ ፀጉሩን አንዴ ዓይኑን ያሻል፡፡ ኩኩሉ እንደሚል
አውራ ዶሮ አንገቱን ከወዘወዘ በኋላ ወደ እኔ ዞር አለና ‹‹ስምህ ናፍቆህ ያውቃል›› አለኝ፡፡
ገረመኝና ‹‹ስሜማ አብሮኝ ነው የሚኖረው፤ ምን ብሎ ይናፍቀኛል›› አልኩት፡፡
‹‹ስምህን ሰጥተህ አታውቅም፤ አሁን ስምህን አልሰጠህም እንዴ›› አለኝ፡፡
ይበልጥ ግራ ገባኝና ‹‹እና ወሰዱት ማለት ነው›› አልኩት ሳቅ እያፈነኝ፡፡
‹‹ታድያስ፤ አሁንኮ ወሳኙ እነርሱ ጋር ያስመዘገብከው ስምህ እንጂ አንተ ጋ ያለው
ስምህ አይደለም፡፡ አንተ እገሌ መሆንህ ቁም ነገር የለውም፡፡ እነርሱ ‹እ-ገ-ሌ› ብለው ሲጠሩህ ነው ሕይወትህ
የሚንቀሳቀሰው፡፡ እኔ አሁን ስሜ ናፍቆኛል፡፡ ስሜ ሲጠራ መስማት፣ ስሜ ሲጠራ አቤት ማለት ናፈቀኝ፡፡››
የእርሱን ስሰማ እኔም ስሜ ይናፍቀኝ ጀመር፡፡ ‹‹ትጠራላችሁ›› አይደል ያሉን፤
እውነትም ስማችንን ወስደውታል ማለትኮ ነው፡፡ ካልጠሩን ቁጭ ብለን መቅረታችን ነው፡፡ የተጠሩት ደግሞ እየተፍነከነኩ ወደ
መስኮቱ እየተጠጉ ነው፡፡ ሰልፉ ሲረዝም፣ ጊዜው ሲሄድ፣ መቀመጥም ሲሰለቻችሁ ደግሞ ስማችሁ ይበልጥ ይናፍቃችኋል፡፡
‹‹እዚህ ብቻ ነው ወይስ ሌላውም ቦታ ወረፋ አለው›› አልኩት፡፡
‹‹ምን እዚህ ብቻ ኑሮህኮ እንደዚሁ ነው፡፡ ስም ትሰጣለህ፣ ትጠብቃለህ፣ ስምህን
ትናፍቃለህ፣ እድለኛ ከሆንክ ትጠራለህ፣ አቤት ትላለህ፣ ወደ ሌላው ምእራፍ ትሻገራለህ፡፡ እዚያም ስም ትሰጣለህ፣ ስም
ትናፍቃለህ፣ ትጠራለህ፣ አቤት ትላለህ፣ እንዲህ እያልክ ትኖራለህ፡፡ አቤት ካላልክ ደግሞ ችግር ነው፡፡ ያልፍሃል፡፡ አሁን ያ
ሰውዬ ስልክ እያወራ አለፈው፡፡ ‹አቤት› ማለት ነበረበት፡፡ አሁን እንደገና ስሙ እየናፈቀው ነው፡፡ ያኛው ደግሞ ስሙ
ቢናፍቀው፣ ቢናፍቀው የሚጠራው አጥቷል፡፡እየደጋገመ ‹ጥሩኝ እንጂ› ይላል፡፡‹ቆይ እንጠራሃለን› ይሉታል፡፡ አሁን አንተን
በስልክ ጠርተውህ ነው አይደል የመጣኸው? አሁን ይኼ ጋቢ ነገር
የለበሰው ሰው ለምን አትጠሩኝም ብሎ ነው ከክፍለ ሀገር የመጣው፡፡ ስሙ ናፍቆት፡፡ ልጁ ደውላ ዕቃ ልኬልሃለሁ አለቺው፡፡ እርሱ
ካሁን አሁን ስሜ በስልክ ይጠራል ብሎ ቢጠብቅ ቀረበት፡፡ ስሙ ሲናፍቀው መጣና ‹እባካችሁ ጥሩኝ› አለ፡፡ እነርሱ ደግሞ
‹ሀገርህ ተመለስና ስንጠራህ ትመጣለህ› ይሉታል፡፡ ስሙ የናፈቀው ሰው መች እንዲህ በቀላሉ ይመለሳል፡፡››
‹‹እውነትምኮ ስም የሚያስናፍቁ አሠራሮች ሞልተዋል›› አልኩት ለመጎትጎት
‹‹ቤት ለማግኘት ትመዘገባለህ፣ ስምህ ይናፍቅሃል፡፡ ጋዜጣ ላይ ወጣ፣ ተለጠፈ፣
በሬዲዮ ተነገረ በተባለ ቁጥር ስምህን ማየት ትናፍቃለህ፡፡ እዚያ ዝርዝር ውስጥ ስታጣው ቅር ይልሃል፡፡ ስኳር ለማግኘት
ትመዘገባለህ፣ ከሻሂው ሱስ ይልቅ ስምህን የመስማት ሱስ ይይዝሃል፡፡ ሥራ ለማግኘት ትመዘገባለህ፣ እንጠራሃለን ስትባል
ትጠብቃለህ፤ ከዚያ ስልክ ባቃጨለ ቁጥር እመር ብለህ ትነሣለህ፤ የሆነ ሰው ስምህን ሲጠራው፣ አንተም አቤት ስትል ለመስማት
ትናፍቃለህ፡፡ ጓደኛህ ደውሎ በቅጽል ስምህ ከጠራህ ትናደዳለህ፡፡ አንተ የምትጠብቀው ‹አቶ እንትና ነዎት› ተብሎ ሲጠራ መስማት
ነዋ፡፡ ››
‹‹ቆይ ግን ለምን ይመስልሃል ስማችን እስኪናፍቀን የምንደርሰው››
‹‹አንደኛ ለምዶብናል፡፡ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ስም ጠሪ መምህር ተመድቦ ስም መጥራት
ተለምዷል፡፡ ዕድር ላይ ይጠራል፤ ፍታት ላይ ይጠራል፤ ዕቁብ ላይ ይጠራል፤ ቡና ለመጠጣት ይጠራል፤ እሥረኛ ለመጠየቅ ይጠራል፤
ቪዛ ለመጠየቅ ይጠራል፤ ስም መጥራት ባህላችን ሆኗል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ስማቸው የሚጠራና የማይጠራ ስላሉ ነው፡፡ ስማቸው
ሊጠራ የሚችል፣ ስማቸው የማይጠራና ስማቸው ሳይጠራ እንደተጠራ የሚቆጠሩ አሉ፡፡ ስማቸው ሊጠራ የሚችለው እንደ
እኔና አንተ ያሉት ናቸው፡፡ ዕድል ካለህ ስምህ ይጠራል፡፡ ስማቸው የማይጠራው ደግሞ አንዳች ምክንያት የሚኖራቸው ናቸው፡፡ ስማቸው
መጠራት የማያስፈልጋቸው ደግሞ ጉዳያቸው በውስጥ የሚያልቅላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ስማቸው የወርቅ ቁልፍ ነው፤ ብዙ
ቢሮዎችን ይከፍታል፤ ወይም ደግሞ የወርቅ ቁልፍ ያንጠለጠለ ስም የሚያውቁ ናቸው፡፡ አንዳንዴኮ ስምን መናፈቅ ይሻላል፡፡ ጭራሽ
ስምህ ይጠፋልኮ››
‹‹አንተ ዋናው ክፉ አትሥራ እንጂ ስምህ ቢጠፋ ምን ችግር አለው? ከባሰ በሕግ መጠየቅ ነው››
‹‹ኖ ኖ ኖ ኖ ኖ እንደዚያ አይደለም፤ ስምህ ከነ ጭራሹ ከመዝገብ ላይ ይጠፋል
እንጂ፤ ስምህ አልተመዘገበም፤ ‹ዳታ› ውስጥ የለም፡፡ ኮምፒውተር ውስጥ አልገባም፤ መዝገብ ላይ አልተገኘም፤ ፋይሉ ጠፍቷል፤
ትባላለህ፡፡ አንዳንዱ ስምማ ይገርምሃል እንደ ቁልፍ ማንጠልጠያ ወልቆ የሚጠፋ ነውኮ የሚመስለው፤ በተመዘገበበት ቦታ
አታገኘውም፡፡ አሁን የእኔ ስም ዕድር ልከፍል ከሄድኩ አንደኛ ነው የሚጠራው፤ ስኳር ልወስድ ከሄድኩ ግን ጭራሽ ሳይጠራ ሊቀር
ይችላል፡፡ ለክፍያና ለመዋጮ ብቻ የታደሉ ስሞች አሉ፡፡ ለመቀበል ብቻ የታደሉ ስሞችም አሉ፡፡ ሁለቱንም ስሞች በየመዝገባቸው
ነው የምታገኛቸው፡፡ አንተ አንዴ እንኳን ስምህ አልጠራ ብሎህ እየናፈቀህ አንዳንድ ሰዎች ሁለትና ሦስት ጊዜ ስማቸው ሲጠራ ስታይ፣
ስም የሌለህ ሁሉ ይመስልሃል፡፡››
‹‹ግን ለሥራና ለስም የታደሉ ሰዎች የሉም››
‹‹ሞልተው፤ አሁን እኛ ሀገር ሊቅ፣ ሳይንቲስት፣ እውነተኛ ነጋዴ፣ ባለሞያ፣ ሥራ
ፈጣሪ፣ ገበሬ፣ ምናምን ለስም ያልታደሉ ናቸው፡፡ ስማቸውን የደመወዝ መክፈያና ግብር ሰብሳቢ ብቻ የሚያውቀው፤ አርቲስት፣
ዘፋኝ፣ ቀልደኛ፣ ደግሞ ለስም የታደሉ፡፡ እስኪ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የአንድ ሳይንቲስት ቤት ዓመት በዓል ሲያከብር አይተህ ታውቃለህ? የአንድ የረዥም ርቀት አሽከርካሪ ቤት ገብቶ ኑሮውን ሲያስቃኝ አይተህ ታውቃለህ? እነዚህ ለስም ያልታደሉ ናቸው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ሥራውን የሠሩት፣ የደከሙት፣ የለፉት
ስማቸው ሳይጠራ መጨረሻ ላይ የሚጨመሩ ቅመሞች ስማቸው ሲጠራ ትሰማለህ፡፡››
ይህንን እያወራልኝ በድምጽ ማጉያ ስም መጥራት ተጀመረ፡፡ አምስት ሰዎች ተጠሩ፡፡
አብሮኝ የነበረው ሰው ግን አልተጠራም፡፡ በድምጽ ማጉያው ‹መሐሪ ተሾመ› የሚል ስም ሲጠራ ከእኛ ፊት ለፊት ባለው ወንበር ላይ
የተቀመጠው ሰው ‹ወንድ ከሆንሽ መሐሪ አስቻለው ብለሽ አትጣሪም›› አለ፡፡
‹‹መሐሪ አስቻለው ብሎ መጣራት የወንድነት መለኪያ ሆነ እንዴ›› አልኩት
‹‹መሐሪ አስቻለው እኔ ነኛ››
No comments:
Post a Comment